Blog

Gospel

«የት እንደማገኝህ አውቃለሁ።» ክፍል ሶስት

December 24, 2018, Author: memher

አስገራሚው የትንሹ ልጄ ታሪክ።

የሰው ልጅ ሁሉ አባታችን አዳም ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ከእውነተኛ አባቱ ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ጠፍቶአል። ነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር «እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ» (ኢሳ.53፡6) ይለናል። አይታወቀን ይሆናል እንጂ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ካለበሰን ክብር ተራቁተናል። እያንዳንዳችን ተቅበዝብዘን ጠፍተናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲነግረን «ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤»ይለናል። (ሮሜ.3፡23) ስለዚህ ሁላችንም ከአባታችን ክብር ጎድለን በዚህች ዓለም እረፍት አጥተን የምንቅበዘበዝ ፍጥረቶች ነን። የርሱን ፈቃድ ተትን የራሳችንን ፈቃድ ተከትለን ጠፍተናል። በአባታችን ቤት ብዙ መብል ተርፎ እያለ የእሪያዎችን ምግብ እየበላን እየኖርን ነው። ፖለቲካው ጥላቻው ሥጋዊነቱ ክፋቱ ዓመጹ ኃጢአቱ እርኩሰቱ ሁሉ የእሪያ ምግብ ነው። ሰው ሲፈጠር ይህንን ሁሉ እንዲመገብ አልተፈጠረም። የእሪያ ምግብና የሰው ምግብ የተለያየ እንደሆነ ሁሉ አሁን ይህች ዓለም ህዝብዋን የምትመግበው ምግብና የእግዚአብሔር ልጆች ምግብ የተለያየ ነው። ይህች ዓለም ከሰይጣን ጋር ተስማምታ እርኩሰትን ዓመጽን ኃጢአትን ነው ሰውን እየመገበችው ያለው። ሰው ሁሉ ሲሰማው የሚውለው ነገር የሚያረክስ ክፉ ነገርን ብቻ ነው። አሁን ሰዎች እየሰሙት እያደረጉትና እየተመገቡት ያለው ነገር ሁሉ የሰይጣን ምግብ ነው። ሰይጣን የረከሰ እሪያ ነው። ምግቡም ሐሰት ክፋት ግድያ አመጽ ኃጢአት ነው። እርሱ የክፉ ነገር ሁሉ ምንጭ ነው። አሁን የዓለም ህዝብ በመስማትም በማየትም በድርጊትም እየተመገበው ወደ ውስጡ እያስገባው ያለው ነገር የዚህ እርኩስ እሪያ የሰይጣንን ምግብ ነው። ይህ እርኩሰት ከመረረንና እንደዚህ ልጅ ወደ አባቴ እመለሳለሁ ብለን በንስሐ ለምንመለስ ግን አባታችን እግዚአብሔር የሰባውን ፍሪዳ አርዶልናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የታረደው የሰባ ፊሪዳ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ በቀራንዮ መስቀል ስለተካሄደው ታላቅ ግብዣ ሲናገር 
«የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።» ይለናል። (ኢሳ.25፡6-9) ይህ ታላቅ ግብዣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ሲሰቀል ለኛ ተፈጸመልን። ሞትን ለዘለዓለም ዋጠልን። በተበደለ ክሶ ወደ ራሱ መለሰን። ከኛ ምንም ሳይጠብቅ በግብዣ ተቀበለን። የጠፋው ልጅ ሲመለስ ከሁሉ ይልቅ የተሻለ ልብስ አምጡለት እንደተባለ እኛም ከሁሉ ይልቅ የበለጠውን አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለበስን። ለእጃችን የፍቅሩ ቀለበት ለእግራችንም የወንጌሉ ጫማ ተደረገልን። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ያልተደሰቱ ሰዎች ነበሩ። የአባት ልብ የላቸውምና ጥፋተኛው በማለፊያ ድግስ አቀባበል ሲደረግለት ሊዋጥላቸው አልቻለም። ስለዚህም ቀራጮችንና ኃጢአተኞችን ይቀበላል ብለው አንጎራጎሩበት። ይህንን በታላቅየው ልጅ ምሳሌ እንዲህ አስቀምጦታል። «ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ፦ ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። እርሱም፦ ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን፦ እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው። እርሱ ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።» (ሉቃ.11፡25-32) ምእራፉን ሲጀምር «ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎችም፦ ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ።» ብሎን ነበር። እንግዲህ እነዚህ ያንጎራጎሩት ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ይህ በእርሻ የነበረው ታላቅ ወንድም መሆናቸው። ይህ ታላቅ ወንድም በጣም ያናደደውና ወደቤት አልገባም ያስባለው የአባቱን ገንዘብ ወስዶ አባክኖ ለመጣው ታናሽ ወንድሙ ታላቅ ግብዣ መደረጉና የሰባው ፍሪዳ መታረዱ ነው። ምክንያቱም በርሱ አስተሳሰብ ይህ ሊደረግ የሚገባው ሁልጊዜ ከትእዛዙ ለማይወጣውና አሁንም እርሻ ውሎ ለመጣው ለእርሱ እንጂ ለወንድሙ አልነበረም። አያችሁ የአባት ልብ ግን የተለየ ነው። ታላቁ ልጁ እንደሚያይ አያይም። የአባት ልብ እንደ አባት ብቻ ነው የሚያስበው። አሁን ለርሱ የሚታየው ልጁ እርሱን ማዋረዱ ወይም ገንዘቡን አባክኖ መጥፋቱ አይደለም። ለርሱ የሚታየው ልጁ በህይወት መገኘቱና ወደ እርሱ መምጣቱ ብቻ ነው። ይህ ግን ለታላቅ ወንድም አይገባም። ምክንያቱም ታላቅ ወንድም የአባት ልብ የለውምና ነው። ይህ ደግ አባት ግን አሁን ክብሩን ተወ አሁንም ዝቅ ብሎ ታላቅ ልጁን «ወጥቶ ለመነው።» ይለናል። ይገርማል እንደ አባትነቱ ሊለመን ሲገባ እርሱ ለመነ። ምን ዓይነት አባት ነው? ኧረ ይገርማል። እግዚአብሔር የሰባውን ፍሪዳ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ አቅርቦ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲመጡ መጋበዙና ንስሐ የገቡትን ሁሉ መቀበሉ ለፈሪሳውያኑና ሕጉን ፈጽመን እንጸድቃለን ብለው ለሚያስቡ አልተዋጠላቸውም ነበር። እነርሱ ሁሉን የሚያዩት ከሥራ አንጻር ብቻ ነው። ጸጋ ማለት ለነርሱ አይገባቸውም። እነርሱ ራሳቸውን የሚያዩት የህጉ አስፈጻሚዎች አድርገው ነውና ሁሉን የሚያዩትና የሚመዝኑት እንደ ህግ አስፈጻሚ ነው። አባት ወይም እናት ልጃቸውን በሚያዩበት መንገድ ማንም ሊያይ አይችልም። ለምሳሌ ስለህይወታችን ስለመልካሙም ስለክፉውም ጎድናችን ከማንም በላይ የሚያውቁት ቤተሰቦቻችን ናቸው። ፖሊስና የህግ አስፈጻሚዎች ስለእያንዳንዱ ቀን ውሎአችን የቤተሰባችንን ያህል ቢያውቁ ኖሮ ምናልባት ብዙዎቻችን ብዙ ጊዜ ተከሰን ፍርድ ቤት የምንቀርብ ይመስለኛል። በቤተሰብ ውስጥ በአባት ዳኝነት በእናት ጠበቃነት በወንድሞችና በእህቶች ምስክርነት የሚያልቁ ብዙ ጉድለቶች አሉ። ቤተሰብ ችግሮችንና ጥፋቶችን የሚያየው በህግ አስፈጻሚዎች ዓይን አይደለም። ለዚህም ነው በህግ አስፈጻሚ ዓይን ቢታዩ በወንጀል የሚያስጠይቁ ብዙ ነገሮች በቤተሰብ ውስጥ መክነው የሚቀሩት። ቤተሰብ ልክ እንደኩላሊት ችግሮችን እያጣራ የሚጠቅመውን እያስቀረ የማይጠቅመውን ወደ ውጭ እየጣለ የሚሄድ አስገራሚ ህያው መንኮራኩር ነው። አባትና እናት በልጆቻቸው ላይ ምንም ዓይነት ጉድለትና ጥፋት ቢያገኙ የመጀመሪያ እርምጃቸው ልጃቸውን ማዳንና ማትረፍ ነው። እኛም ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጋር ያለን ግንኙነት እንደዚህ ዓይነት ነው። እግዚአብሔር ከቅዱስ ባሕርዩ የተነሳ ኃጢአትን በእጅጉ ቢጠላም እኛን ግን በእጅጉ ይወደናል። እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ርህራሄና ፍቅር በእናት ፍቅርም መስሎ አሳይቶናል። እናት አንጀትዋ አይቆርጥም። ልጅዋ በምንም አይነት ጥፋትና ውድቀት ይገኝ ሁልጊዜ ትራራለች። በእናትና በልጅ መካከል ያለው ቁርኝት እጅግ የጠበቀ ነው። የዚህ ዘመን ትውልድ እናትን ሲሳደብ ስትሰሙ ምን ያህል የተረገመ ትውልድ እንደሆነ መለኪያው ነው። የእግዚአብሔር ቃል የፍቅር መለኪያ አድርጎ ያስቀመጣትን እናት ስትነካ ማየት ያሳዝናል። እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር ሲናገር «ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።» (ኢሳ.49፡14-15) እንደዚህ የፍቅር ተምሳሌት የሆነች እናት ትረሳ ይሆናል ተባለች የአባታችን የእግዚአብሔር ፍቅር ግን በኛ ላይ የጸናች ናት። በቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር ከሚጠራባቸው ስሞች አንዱ የስላሴ መጠሪያ የሆነው ቅድስት ስላሴ የሚለው ስም ነው። በተለመደውና በትክክለኛው አማርኛ ካየነው «ቅድስት» የሚለው የሴቴ አንቀጽ ስለሆነ ለቅዱሳን ሴቶች ወይም ደግሞ የበጉ ሙሽራ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ብቻ የምንጠቀምበት ነው። አባቶቻችን ግን ይህንን ሁሉ የአማርኛ ህግ ጥሰው ስላሴን ቅድስት ስላሴ ይሉታል። ይህ ለምን እንደሆነ የድሮ አባቶች ሲናገሩ እግዚአብሔር የእናት አንጀትን የሚመስል ርህራሄ ያለው አምላክ ስለሆነ ርህራሄውን ለመግለጽና ለማሳየት ተብሎ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ። በእርግጥም በቃሉ ውስጥ እግዚአብሔር በተለያየ ቦታ ይህንን ባህርዩን ሲገልጥ በደንብ እንመለከታለን። ለምሳሌ ስለኤፍሬም ሲናገር እንዲህ ይላል። «ኤፍሬም፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም ብሎ ሲያለቅስ ሰማሁ። በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ (ኤር.31፡18-20) ይገርማል እግዚአብሔር አባታችን ስለ እኛ አንጀቱ የሚታወክ አምላክ ነው። እንዲሁ በአምላክነቱ ብቻ በሁሉን ቻይነቱ ብቻ ህይወታችንን የሚያውቅ ሳይሆን አንጀቱ የሚታወክልን የሚራራልን አባት ነው። እንግዲህ ወደ ተነሳንበት ታሪክ ስንመለስ ኢየሱስ ክርስቶሰ ወደርሱ ይመጡ የነበሩትን ኃጢአተኞች በዚህ አንጀቱ ነበር የሚራራላቸው። ተጎሳቁለው ተራቁተው ነው የሚታዩት። በመልኩ የፈጠረውና የርሱን ክብር ለብሶ የነበረ ሰው እንደዚያ ተራቁቶ ሲያይ ራራለት። ያ በምሳሌው የቀረበው አባት ልጁ ተጎሳቁሎ ሲያይ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጥታችሁ አልብሱት እንዳለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርቃናችንን በጸጋው ሊያለብስ ረሐባችንን በሥጋውና በደሙ ሊያረካ መጣልን። በነቢዩ «እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል።» ተብሎ እንደተነገረ (ኢሳ.61፡3) በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ ሊሰጠን መጣ። ይህ ሲገባን እንደ አዳምና ሄዋን እርቃናችን መሆናችን አስፈርቶን ከርሱ አንሸሽም ይልቅስ እንዲያለብሰን ወደርሱ እንቀርባለን።
ብዙ ጊዜ ወንጌሉ በትክክል ያልገባቸው ሰዎች ወይም ትክክለኛውን ወንጌል ያልሰሙ ሰዎች ኃጢአተኛ መሆናቸውን ሲያውቁ ከእግዚአብሔር ይሸሻሉ። እኔ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ወደርሱ መቅረብ አልችልም ብለው ይርቃሉ። ያንንም እንደ ትክክለኛ እርምጃ ይወስዱታል። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ኃጢአተኛ ሆኜ ወደርሱ መቅረብ አልችልም ይላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘው ወቅት ቅዱስ ጴጥሮስም ያደረገው ይህንኑ ነበር። ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ጴጥሮስን ታንኳ ለምኖ ታንኳዋ ላይ ተቀምጦ ህዝቡን ካስተማረ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ዓሣ እንዲያጠምዱ ነገራቸው። እነርሱም ሌሊቱን ሁሉ ሲያጠምዱ አድረው ምንም እንዳልያዙና አሁን ግን እርሱ ስላለ ብቻ እንደሚያጠምዱ ተናግረው መረባቸውን ሲጥሉ እጅግ ብዙ ዓሳ ያዙ። ከዚያ በኋላ ነበር ቅዱስ ጴጥሮስ የሚከተለውን የተናገረው «ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን፦ አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።» (ሉቃ.5፡8-11) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ የወሰደው እርምጃ ብዙዎቻችን የምንወስደውን ነው። ኃጢአተኛ መሆናችንን ስናውቅ ከእግዚአብሔር እንርቃለን። እግዚአብሔር ግን የእኛ መፍትሄ ያለው እርሱ እንደሆነ ስለሚያውቅና ስለሚወደን ወደርሱ እንድንቀርብ ነው የሚፈልገው። አዎ እራቁታችንን ነን ነገር ግን የክብር ልብሳችን ያለው በአባታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። አዎ ረሃብተኞች ነን ነገር ግን መብላችን ያለው በርሱ ዘንድ ብቻ ነው። አዎ ኃጢአተኞች ነን ነገር ግን ከኃጢአታችን ሁሉ የሚያነጻን ክቡር ደም ያለው በርሱ ዘንድ ብቻ ነው። ስለዚህ እንደ እኔ ኃጢአታችሁ እጅግ የከበደባችሁ እራቁትነት ባዶነት የሚያሰቃያችሁ እንደ ጠፋው ልጅ ለእሪያ የሚቀርበውን አሰር እንኳ የሚሰጣችሁ አጥታችሁ በረሃብ እየጠፋችሁ ያላችሁ ወገኖቼ ልክ እንደጠፋው ልጅ ወደ ልባችን እንመለስ «ወደ አባቴ እሄዳለሁ» እንበል። ይህ ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ በመጸጸት ወደ አባቴ እሄዳለሁ ሲል እጅግ የተራበ የተጎሳቀለ ጌጠኛ ልብስ የሌለው ለእግሩ ጫማ ለእጁ ቀለበት የሌለው ነው የሆነው። እነዚህን ሁሉ ካሟላሁ በኋላ ጥሬ ግሬ ልብስ ከቀየርኩ በኋላ እሄዳለሁ አይደለም ያለው። ይህን ቢል ኖሮ መቸም አይመለስም ነበር። ምክንያቱመ ይህን ሁሉ ማሟላት አይችልምና። ስለዚህ ከነ እርቃኑ ከነ ረሀቡ ነው የመጣው። አባቱም እርቃኑን መዋረዱን ረሃቡን ሲያይ አልፈረደበትም ይልቅስ እጅግ ራራለት። ዛሬም አባታችን እግዚአብሔር ለሁላችንም እንደዚሁ ነው። የጠፋው ልጅ አባት ገና ከሩቅ ሲመጣ አይቶ እንዳዘነለት እኛም ከእግዚአብሔር እጅግ ርቀን እያለን እንኳ ይራራልናል። አሁን ከእግዚአብሔር በጣም በራቀ ሕይወት ውስጥ ሆናችሁ ይህንን ቃል የምታነቡ ወገኖቼ ሁሉ ያላችሁበት ሁኔታ ላይ እግዚአብሔር እያያችሁ ነው። በፍቅሩ ገመድ ወደርሱ ጎትቶ ለማቅረብ ሁልጊዜ ልባችንን ይቀሰቅሳል። የጠፋው ልጅ ከአባቱ ቤት ቢጠፋም አባቱ ግን ከልቡ አልጠፋም ነበር። ስለዚህ ወደ አባቴ እመለሳለሁ አለ። እኛም ወደ ልባችን ብንመለስ ወደ አባቴ እመለሳለሁ ማለታችን የማይቀር ነው። የአባትነት ፍቅሩ በልባችን ውስጥ እየፈሰሰ ወደ አባቴ እመለሳለሁ እንደንል ሁላችንን ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።
መምህር ጸጋ።