Blog

Gospel

“የት እንደማገኝህ አውቃለሁ። ” ክፍል አንድ

December 19, 2018, Author: memher

“I know where to find you.”

አስገራሚው የትንሹ ልጄ ታሪክ።

አስተውለን ካየን በኛና በልጆቻችን መካከል ያለው ቁርኝት በእኛና በእግዚአብሔረ መካከል ያለውን ግንኙት በጥቂቱም ቢሆን የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ስለሰው ልጆች ያለውን የአባትነት ፍቅርና ልብ ለማስረዳት ወላጆችንና ልጆችን ምሳሌ አድርጎ የሚጠቀመው። ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል አስራ አንደ ላይ አባታችን እግዚአብሔር ምን ዓይነት አፍቃሪና ርህሩን እንደሆነ ለማስተማር እንዲህ በሎ ነበር።

«እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።

የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።

አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን?

ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?

እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?» ሉቃ.11፡9-13

እንደዚሁም በዚሁ በሉቃስ ወንጌል አስራ አምስተኛው ምእራፍ ላይ ታናሹ ልጁ ስለጠፋበት አባት ምሳሌ በማቅረብ ያ የጠፋው ልጅ ተመልሶ ሲመጣ ምንም እንኳ አባቱን ንቆና ትቶ የሄደ ልጅ ቢሆንም ሲመለስ ግን ምን ዓይነት ታላቅ ግብዣ እንዳደረገለት ይነገረናል። (ሉቃ.15፡11-32)

ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሁሉ ምሳሌ እያቀረበ ያስተማረው እርሱ ከሰማይ እኛ በኃጢአት ወድቀን ስለጠፋንበትና እርሱ ደግሞ እኛን ሳይመለስ እንዳይኖር የአባትነት ፍቅሩ ስላስገደደው ዙፋኑን ትቶ ሊፈልገን መምጣቱን ለማስረዳት ነበር። እነዚህን ሁሉ ምሳሌዎች ያቀረበበት ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ራሳቸውን እንደ ጻድቃን የሚቆጥሩ ፈሪሳውያንና ካህናት አንተ ቅዱስ ከሆንክ እንዴት ከኃጢአተኞች ጋር ትውላለህ? የሚል ጥያቄ ደጋግመው ያቀርቡለት ስለነበረ ነው። እርሱም የመጣው ኃጢአተኞችን ሊፈልግ እንደሆነና በጉ የጠፋበት ሰው ለማግኘት እንደሚፈልግ ሁሉ እርሱም የሰው ልጆችን ሊፈልግ እንደመጣ በብዙ ምሳሌ አስረዳቸው። ካቀረበላቸውም ምሳሌ ሌላው መቶ በጎች ስላሉት ሰው ሲሆን ይህ ሰው ከመቶ በጎች አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኝ በጎች አሉኝ ብሎ ያንን አንድ በግ እንደማይረሳውና ይልቅስ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ አንዱን ፍለጋ እንደሚሄድ ባገኘውም ጊዜ ተሸክሞ እንደሚያመጣው የተናገረው ምሳሌ ነው። «ኃዲጎ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ» እያልን የምናዜመውም ለዚህ ነው። (ሉቃ.15፡3-7) እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ምሳሌ እንደምንረዳው እኛን ካለገኘ ልቡ የማያርፈው መልካሙ እረኛ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የጠፋነውን የሰው ልጀችን ፍለጋ ክብሩንና ዙፋኑን ትቶ እንደመጣ ሲሆን ነገር ግን በሚቃወሙትና ራሳቸውን ጻድቃን እንደሆኑ ወይም ደግሞ በራሳቸው ጽድቅ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንደሚችሉ የሚያስቡ ሰዎች ዘንድ ይህ ድርጊቱ ተቀባይነትን አላገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሊፈልጋቸው ወዳሉበት የዓለም ምድረ በዳ ቢመጣ እኛ ራሳችን ለእግዚአብሔር እንገኝለታለን በራሳችን ጥረትና ጽድቅ ወደ ክብራችን እንመለሳለን ብለው ሞገቱት። በሌላ አማርኛ የጠፉት እነርሱ መሆናቸውን ረስተው ራሳቸው እግዚአብሔርን ፈልገው እንደሚያገኙት አሰቡ አመኑ ማለት ነው። ወንጌል እንደሚያስተምረን ግን ሰው እንደጠፋው በግ ነው። የጠፋውን በግ ደግሞ ፈልጎ ያገኘው እረኛው ነው እንጂ በጉ አይደለም እረኛውን ፈልጎ ያገኘው። ብዙዎቻችን ግን ይህ ወንጌል ስላልገባን ሊፈልገን የመጣውን እረኛ ድምጽ ሰምተን በትከሻው ሊሸከምን እጆቹን ሲዘረጋ በእምነት እንደመቀበል እኛ ራሳችን ጥረን ግረን በጽድቃችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንደምናገኘው እናስባለን። በብዙ ክርስቲያኖች ያለው በጣም መሠረታዊ የእይታ ልዩነት ይህ ነው። ብዙዎቻችን እንዴት እንደምናስብ ለማስረዳት አንድ በራሴና በትንሹ ልጄ መካከል የተፈጸመን አስቂኝና አስተማሪ ታሪክ ልንገራችሁ። ልጄ የአራት ዓመት ተኩል ልጅ እያለ ብዙ ሰዎች ወደሚሰበሰቡበት ዓመታዊ የሮዲዮ በዓል ይዤው ሄድኩ። ይህ በዓል ከመላው ቴክሳስ ብዙ የከብት አርቢዎች የሚሰበሰቡበት በዓል ሲሆን በዓለም ላይ ካሉ ታዋቂ ሰው ሰራሽ ድንቆች መካከል በሚቆጠረው አስተሮዶም ወይም ኢነርጂ ስታድዮም በሚባለው ቦታ በየዓመቱ የሚደረግ ነው። እንግዲህ በዚህ ፌስቲባል ላይ ብዙ ህዝብ ስለሚገኝ ህጻናት እንዳይጠፉ ጥንቃቄ ይደረጋል። አንዳንድ ወላጆች እንዲያውም በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ትንንሽ ልጆቻቸውን ወገባቸው ላይ ገመድ በማሰር ነው የሚይዙአቸው። እንግዲህ እኔም የአባት ልቤ አስገድዶኝ ትንሹ ልጄን በገመድ ባላስረውም እጄን ይዞ እንዲራመድ ደጋግሜ ጠየቅኩት። እርሱ ግን የህጻንነት ፈንጠዝያው ግድ እያለው እጄን ለቆ በራሱ እየፈነጠዘ መሄድ ስለሚፈልግ እጁን መያዜን አልወደደውም። ከዚያ እርሱን ላለማስከፋት ብየ እጁን ለቀቅኩት በቅርብ ርቀት እከተለው ጀመር። ትንሽም ሳይቆይ ተሰወርኩበት። እኔ በርቀት እያየሁት ነው እርሱ ግን አያየኝም ስለዚህ ፊቱ መለዋወጥና መጨነቅ ሲጀምር ይታየኛል። ያች ትንሽዋ ፊቱ የበለጠ አነሰች። ፊቱ ክፍት አለው። ከዚያም ወደ ላይ ቀና እያለ በአጠገቡ ያሉትን ሰዎች ፊት ማማተር ጀመረ። ነገር ግን ቀና ባለ ጊዜ ሁሉ በብዛት የሚያየው ነጮችን ነበርና እኔ እንዳልሆንኩ ወዲያ እየተረዳ ወደሌላው ደግሞ ያማትራል። ይህ ከአስራ አምስት ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ የተካሄደ ትንሽ ድራማ ነበር። እኔም እንዳያየኝ ራሴን እየደበቅኩ እከተለዋለሁ። በመጨረሻ ተስፋ እንደቆረጠ በሚያሳይ መልኩ ቀና እያለ የሰዎችን ፊት ማየት ተወና መሬት መሬት እያየ በዚያች የህጻን አንደበቱ የሆነ ራሱ የፈጠረውን የዜማ እንጉርጉሮ እያንጎራጎረ በሚተራመሰው ህዝብ መሃል ይሄድ ጀመር። ድክም ብሎት ሳየው አሳዘነኝና ከዚህ በላይ መታገስ ስላልቻልኩኝ ጠጋ ብየ እጁን ያዝኩት። ወዲያውኑ ፊቱ ፈክቶ አባቢ ብሎ እቅፍ እንዳረገኝ አየህ እጄን ያዘኝ ካለዚያ ትጠፋለህ ብየ እኮ ነበር። አሁን አየኸው አይደል? በማለት ስላገኘሁት ያመሰግነኛል ከስህተቱም ይማራል ብየ ስጠብቅ ምን ያለ ይመስላችኋል። በእንግሊዘኛ ነበር የተናገረውና እንዲህ አለ I know where to find you የት እንደማገኝህ አውቃለሁ ነበር ያለው። ይህን ስሰማ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ በሳቅም በግርምትም ካየሁት በኋላ ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱስ ልቤን ያዞረው ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችን ነበር። ብዙዎቻችን እኮ ለእግዚአብሔር እንደርሱ ነው የሆንበት። ተመልከቱ ገና አምስት ዓመት ያልሞላው ልጄ መሸነፍን አልፈለገም ። እንደዚያ ጨንቆት እንዳልነበር እኔ ባላገኘው ባልከተለው ኖሮ ፈጽሞ ሊያገኘኝ እንደማይችል እያወቀ ግን መሸነፍን አልፈቀደም። ራሱ ፈልጎ ሊያገኘኝ ይችል እንደነበር ነገረኝና አስገረመኝ። እኛም እንደዚህ ነው እየሆንን ያለነው። አባታችን አዳም በዲያብሎ ከሳተና ከሞተ ጀምሮ ከእግዚብሔር ክብር ጎድለናል ጠፍተናል። ለብዙ ዘመናት በጨለማ በምድረ በዳ ተንከራትተናል። የሰው ልጅ እየኖረ ያለው ሕይወት በጨለማ የተዋጠ የምደረ በዳ ኑሮ ነው። ስለለመድነው ምንም አይመስለነው ይሆናል እንጂ በዚህች ምድር ያለው ኑሮ ጥላቻው ጦርነቱ ክፋቱ የሰው ልጅ ምን ያህል በጨለማ እየተመላለሰ እንዳለ የሚያሳየን ነው፡ ይህ ሰው ሊኖርበት የተፈጠረ ስርዓት አይደለም። ስለዚህ ሰው ከእግዚብሔር ጠፍቶ በምድረ በዳ ነው እየተመላለሰ ያለው፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ደግሞ የዘላለም አምላክ የሆነው መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩንና ዙፋኑን ትቶ ሊፈልገን እንኳ ሲመጣ I know where to find you እያልን እየሞገትነው መሆኑ ነው። አዲስ ኪዳን ማለት እግዚአብሔር ራሱ ሰውን ፍለጋ የመጣበት ዘመን ነው። እንደ ድሮው በነቢያት በመላእክት አይደለም የፈለገን ራሱ ነው ሊፈልገን የመጣው። ነቢዩ ኢሳይያስ ሲተነብይ ሲተነብይ አንድ ቀን ከአእምሮው በላይ የሆነ ነገር ሰማ። ይህን ከመስማቱ በፊት እግዚአብሔር ለህዝቡ የሚናገረውን ነበር የሚያስተላልፈው ሰባተኛው ምእራፍ ላይ ሲደርስ ግን ራሱ እግዚአብሔር ሊመጣ እንደሆነ ሰማ። ይህን ሲሰማ ያለውን ተመልከቱ «እርሱም አለ፦ እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» (ኢሳ.7፡13-14) የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሔር በነቢያቱ የሚልከውን መልእክት አልሰማ እያሉ ነቢያቱን አድክመዋቸው ነበር። አሁን የሰማው ደግሞ ከዚያም አልፎ ራሱ አምላካቸው ከድንግል ሊወለድ እንደሆነ ስለሆነ «ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ?፤» በማለት በግራሞት ጠየቀ።

እውነትም ይህ ያስገርማል። የኛ አምላክ እንደ ሌሎች ሰዎች አማልክት በማይታወቅ ስፍራ የሚኖር በርቀት ብቻ የሚያውቀንና የምናውቀው አይደለም። ሰው ገና ሲፈጥረው በገነት ከርሱ ጋር ይኖር ነበር። የርሱ ቤተሰብ አድርጎ ነው በመልኩ የፈጠረው። ከወደቀም በኋላ ለርሱ ያለው ፍቅር አስገድዶት ራሱ ሊፈልገው መጣ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእብራውያን መልእክቱን ሲጀምር «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤» ይለናል። (እብ.1፡1-2) አዎ በአዲሱ ኪዳን እግዚአብሔር በአንድ መንገድ ያውም በራሱ ነው የተናገረን። ራሱ ነው ሊፈልገን የመጣው። እኛ አይደለንም ፈልገን ያገኘነው እርሱ ነው ፈልጎ ያገኘን። እኛ አይደለንም በጽድቃችን ወደርሱ የምንደርሰውና የደርስነው እርሱ ነው ከወድቅንበት ያነሳን። እርሱ ነው በምድረ በዳ ስንቅበዘበዝ ደርሶ የተሸከመን። እኛ ግን ብዙ ጊዜ ይህንን የርሱን ሥራ ላለመቀበል የምንደረድረው ትምክህት አለን። የራሴን ልጅ ምሳሌ አድርጌ ያቀረብኩላችሁ ይህንን በሚገባ እንድናስተውለው ነው። አንዳንድ ጊዜ ከኃጢአታችንና ከውድቀታችን ይልቅ አለን የምንለው ጽድቅ ነው ከእግዚአብሔር የሚለየን። የአይሁድ ህዝብ የደረሰባቸው ይህ እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያስተምረናል።

«ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።» (ሮሜ.10፡1-4) እጅግ ያሳዝናል ሰው በጽድቁ ሲጠፋ። የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ገፉ። ሊፈልጋቸው የመጣውን ሰቀሉት። ልፈልጋችሁና ላገኛችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ላስታርቃችሁ መጣሁ ቢላቸው we know where to find you አሉት። በርሱ ሥራ ሳይሆን በራሳቸው ጽድቅና ጥረት ወደ እግዚአብሔር ሊደርሱ የማይጨርሱትን ጉዞ ጀመሩ። ይህ ጉዞ ግን ወደ እግዚአብሔር አላደረሳቸው። ዛሬስ እኛ ሊፈልገን የመጣውን እረኛ እየሰማነው ይሆን? በዚህች ዓለም ምደረ በዳ የጠወላለግነውን በብዙ ግፊያ መካከል አባት አጥተን የምንኖረውን ከርሱ ተለይተን ልባችን በሐዘን የጠወለገውን ሊፈልገን ሊያገኘን ከሰማይ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በመንፈሱ በወንጌሉ እየጠራን ነው። አጠገብህ አጠገብሽ አለሁ እናንተ ባታዩኝም እኔ አያችኋለሁ እያለ እየጠራን ነው። ልጄ ከኔ በጠፋ ጊዜ እርሱ ባያየኝም እኔ ግን እያየሁት ነበር። እርሱ ስለማያየኝ ብዙ ተጨነቀ የብዙ ሰው ፊት ላይ አማተረ እኔ ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ ዓይኖቼ በርሱ ላይ ነበሩ። አባታችን እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ዓይኖቹ በኛ ላይ ናቸው።

እርሱ እያየን ነው የምናርፈው ግን የሚያየንን ስናየው ነው። የአብርሃም ባሪያ አጋር ልጅዋን ይዛ ከቤት በተባረረች ጊዜ በምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። የሚጠጣ ውሀ በሌለበት ምድረ በዳ ከልጅዋ ጋር ለሞት ቀረበች፡ ልጄን ሲሞት አልየው ብላም ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔር ግን ያያት ነበር። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።» (ዘፍ.21፡16-19) እጅግ ርህሩህ የሆነው እግዚአብሔር በምድረ በዳ ልጅዋን ይዛ ስትንከራተት በዓይኖቹ ይመለከታት ነበር። ለርስዋ እጅግ ቀርቦ የሚታያት ሞት ቢሆንም የውሀ ምንጩ ግን በአጠገብዋ ነበር። እግዚአብሔርንና በረከቱን የማናየው በዙሪያችን ስለሌለ ሳይሆን ዓይናችን ስላልተከፈተ ነው። ዓይናችን ሲከፈት ግን አባታችን ምንጊዜም የማይተወንን እግዚአብሔርን እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለአጋር ምህረቱን ያሳየው በዚህ ስፍራ ብቻ አይደለም ። ከዚህም ቀደም ብሎ ተገልጦላት ነበር። ያንጊዜም እንዲህ በማለት ነበር የተናገረችው።

«እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው።) (ዘፍ.16፡13-14)

አዎ እኛም እናርፍ ዘንድ እግዚአብሔርም እናመሰግን ዘንድ ዓይኖቻችን ይከፈቱ። ያን ጊዜ ኤልሮኢ የሚያየኝን አየሁት እንላለን። የሚያየንን ስናየው ሕይወታችን ይለወጣል። ተቅበዝባዥ የነበረው ያረፈ የደረቀ የነበረው ለምለም ተስፋ ቢስ የነበረው ባለ ተስፋ ይሆናል። እግዚአብሔርን ካየነው የከበበን ፍርሃት ይገፈፋል። በእናቱ እቅፍ እንዳለ ህጻን ልጅ እርፍ እንላለን።

ያእቆብ ከወንድሙ ከኤሳው በሸሸ ጊዜ የሆነውን ተመልከቱ። ወደ ሎዛ ሲደርስ ጸሐይ ገባችበት። ከዚያም ብቻውን እንዳለ እየተሰማው ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ። ግን እውነት ብቻውን ነበር? ዓይኖቹ ሲከፈቱ ብቻውን እንዳልነበረ አወቀ። ቃሉ እንዲህ ይላል።

«ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ።

ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።

እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤

ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ።

እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።

ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፦ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ።

ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።

ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት። ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ።» (ዘፍ.28፡10-19)

ይህ እጅግ የሚያስገርም የዘመናት ታሪክ ነው። ይህ ብላቴና ከወንድሙ ከኤሳው ኮብልሎ ለማምለጥ እንጂ እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ይገናኘኛል ብሎ አስቦ አልነበረም። በርሱ ቤት በማያውቀው እንግዳ ምድር ብቻውን ተኝቶአል። የተኙ ልጆቻችንን እየተመለከትን ደስ እንደሚለን እግዚአብሔርም ይህንን ብላቴና እየተመለከተ ደስ ብሎት ለርሱ ያለውን ሐሳብ ያሳየው ጀመር። መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተትክሎ እግዚአብሔር በላዩ ላይ ቆሞበት መላእክት ሲወጡና ሲወርዱበት ተመለከተ። እግዚአብሔርም እንሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ በማለት የተኛባትን ምድር ለርሱና ለዘሩ እንደሚሰጥ ዘሩን እንደሚያበዛና እንደሚባርክ በሚሄድባት ምድር እንደሚጠብቀው ነገረው። ያእቆብ ከእንቅልፉ ሲነሳ እጅግ በመገረም እንደዚህ አለ። «በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ። ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።» ሲተኛ ይህንን አላወቀም ነበር። የሚያየውን እግዚአብሔርን የሚያይ አልነበረም። ሲነሳ ግን ይህ ሁሉ ተቀየረ። የሚያየውን እግዚአብሔርን አየው። ከዚያም ብዙ ነገር ተቀየረ። የያዘውን ዘይት ድንጋዩ ላይ አፈሰሰና የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን ድንጋይ ለእግዚአብሔር ቤት መሠረት ይሆን ዘንድ ሀውልት አድርጎ አቆመው። የከተማይቱንም ሰም ከሎዛ ወደ ቤቴል ቀየራት። ቤቴል ማለት የእግዚአብሔር ማለት ነው። ዓይኑ ከመከፈቱ በፊት የሚያየውን አምላክ ከማየቱ በፊት ባዶ የነበረው ሥፍራ አሁን ግን እግዚአብሔር ስለተገለጠለት ቤቴል ሆነ። በዚህም የምንማረው ያለንበትን ማንኛውንም ሁኔታ ለውጦ ሌላ ሊያደርገው የሚችለው የእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ነው። እኛና አባታችን ስንገናኝ የሚያየንን ስናየው የከበበን ሁሉ ይለወጣል። በሰው ዓይን ሲታይ ደረቅ ምድረ በዳ የሚመስለው በኛ ዓይን ግን ለምለም መሰማሪያ ይሆንልናል።

እኛ የሰው ልጆች ከክብሩ ጎድለን ህልውና ጠፍቶብን በዚህች ግርግርዋ በማያልቅ ዓለም እየተመላለስን ነው። ከርሱ ርቀን የኖርንበት ዘመን ሁሉ አድካሚ ነው። እጅግ ዝለናል። ያሳርፈናል ወዳልነው ነገር ብዙ ጊዜ ዘወር ዘወር ብለን አማትረናል። ነገር ግን በአባታችን በእግዚብሔር ከመገኘትና በርሱ እቅፍ ከመግባት ሌላ የሚያሳርፈን ነገር የለም። ማረፍ ያለው በአባታችን እቅፍ ብቻ ነው። ቅዱስ ዳዊት እንደዚህ አለ፡

«ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?

ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።

እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።

እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።

ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።

እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።» መዝ.121

እኛም ወደ ብዙ ተራሮች ዓይናችንን አንስተናል። ልጄ አባቱ የመሰለውን ሁሉ ቀና እያለ እንዳየ እኛም እረፍት የሚያስገኝልን የመሰለንን ሁሉ ቀና ብለን አይተናል። ነገር ግን በዚያ እረፍት የለም። በገንዘብ በብልጽግና በክብር በዝና በምንም እረፍት የለም። የሰው ልጅ እረፍቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ስለዚህ እኛም እንደ ንጉሥ ዳዊት ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እንበል። መልካሙ እረኛ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ

«እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።» በማለት የፍቅር ጥሪውን እያሰማን ነው። (ማቴ.11፡28-30)

እኛም ትዕቢታችንን በራሳችን ጽድቅና ሥራ መመካታችንን ትተን «የት እንደማገኝህ አውቃለሁ» የሚለውን የትምክህት ቃል ትተን መልካሙ እረኛየ ሆይ ፈልገህ ስላገኘኸኝ አመሰግንሃለሁ ። እኔ ባላየሁህ ጊዜ ሁሉ ስላየኸኝ አመሰግንሃለሁ። ዓይኖችህ ከኔ ተለይተው ስለማያውቁ አመሰግንሃለሁ እንበለው።

ይቀጥላል።

በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንኩ

መምሕር ጸጋ።